ከመቃብር የወጣው የታሪክ ምስክር-ጎረባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን
የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ዶክተር አሥራት ዓፀደወይን፣ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ጋሻው አንዳርጌ፣ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር መሰረት ካሴ ፣አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ እንዲሁም የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህራን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት አቅራቢያ ከሰሞኑ በቁፋሮ የተገኘውን የጎረባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅሪት ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

ጎረባ ጊዮርጊስ የኪነ ህንፃ ፍርስራሽ፣ ንዋዬ ቅዱሳንና ዕደ ጥበባት በቁፋሮው የተገኙ ሲሆን መቸ እንደተሰሩ፣ በማን እንደተሰሩ እንዲሁም እንዴት እንደተቀበሩ ለማረጋገጥ ጥናት ይጠይቃል ፡፡የተገኘው የሰዎችም አፅም ራሱን የቻለ ምርምር ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ ነገሮችን ያመላክታል ብለን እናስባለን፡፡ምናልባትም እስከ 500 ዓመት ወደኀላ ሊወስደን ይችላል፡፡ ግምቱ በሳይንስ የሚፈታ ይሆናል፡፡

ከወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ውበቱ መስፍን፣ ከዩኒቨርሲቲያችን ታሪክና ቅርስ ምሁራን፣ ከወረዳውና ክልሉ የቅርስ ጥናት ባለሙያዎች እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር “ምን እናድርግ” በሚለው ጉዳይ ላይ ከፍተኛ አመራራችን አጭር ምክክር አድርጓል፡፡

ዶ/ር አስራት በመሩት ውይይት “የአባቶችን አፈ ታሪክ በአፅንኦት ተረድታችሁ ትናንትን ፍለጋ አካፋና ዶማ አንስታችሁ ከአያቶቻችን የእጅ ጥበብ ፣ ተጨባጭ አሻራ ጋር ላስተዋወቃችሁን፣ ይህን ቅርስ ቆፍራችሁ እዚህ ላደረሳችሁ አርሶ አደሮች አንድናቆቴ ይድረሳችሁ” ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በተደራጀ መልኩ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ ነገ ዛሬ ሳይባል ወደ ተግባር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ዶ/ር ጋሻው በበኩላቸው “አካባቢው ወደ ላይ ግዙፍ፣ወደ ታች ጥልቅ የታሪክ ፀጋ አለው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የምናየውን ማስተዋል፣ የተሰወረውን መፈለግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እውቀታችን ተግባር ላይ እናውለው” ብለዋል፡፡
አቶ ውበቱ መስፍን “ብዙ ታሪኮች ሲነገሩን የተለመደ ነው እያልን ትኩረት አንሰጠውም ነበር፣ነገር ግን በአርሶ አደሮች ጥረት ይህን ቅርስ አግኝተናል” በመሆኑም ለመሬቱ ባለቤት ምትክ መስጠትና ጥበቃ መድቦ ቅርሱን ለመንከባከብ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የጎረባ ጊዮርጊስን ታሪካዊነት አስጠብቆ ለማቆየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን የቤት ስራ ተከፋፍለው ተለያይተዋል፡፡ ከተረዳነው ቁርጠኝነት አኳያ ተግባራዊነቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እውን እንደሚሆን እናምናለን፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ
ሚያዚያ 23/2012 ዓ.ም



