ፕሮፌሰር ንብረት ሞገስ
ድካምዎ ፍሬ አፍርቶ ለሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ስለበቁ እንኳን ደስ አለዎት፡፡
የደንቢያው ቡቃያ ፣ በቆላድባና ጎርጎራ ትምህርት ቤቶች ተኮትኩተው፣ በአዲስ አበባው ኮከበ ጽብሃ በእውቀት ታንፀዋል፡፡ የያኔው እምቦቀቅላ ያሁኑ ፕሮፌሰር ንብረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሀዋሳ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በእንስሳት እርባታና መኖ ዲፕሎማ አገኙ፡፡ እንደተመረቁ የሥራን ዓለም የተዋወቁት በግብርና ሚኒስቴር ነበር፡፡ በእውቀትና ምግባር የደረጁት ጎልማሳ ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኀላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ሞስኮ አቀኑ፡፡ ከሞስኮ መልስ ያገኙትን እውቀትና ልምድ ለመስሪያቤታቸው በሚበጅ፣ ለሀገራቸው በሚጠቅም መልኩ በተግባር አሳይተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ንብረት ሞገስ በ1998 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ትውልድ እንደ እርሳስ መቅረፅ፣ ተተኪ ማፍራት ደስታቸውን አበዛው፡፡
ማስተማር የመማር ፀጋን አጎናፀፋቸው፡፡ በቬተርናሪ ኢፒዲሞሎጅ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡ የአስተሳሰብ አድማሳቸው ሰፋ፡፡ ለማሪዎቻቸው የሚያካፍሉት እውቀት ጨመረ፡፡ ልፋታቸው በፍሬ ሲገለፅ ደስ ተሰኙ፡፡ ሌላ ጉዞ፣ ሌላ ከፍታ ማየት ፈለጉ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደብረ ዘይት እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዓይናቸው አረፈ፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በቴሪዮጀኖሎጅ አገኙ፡፡
ፕሮፌሰር ንብረት ሞገስ የቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማርና ማማከር አንቱታን አትርፈዋል፡፡ የደቀ መዛሙርቱ መልካም አርአያ ናቸው፡፡
ፈለጋቸውን ለሚከተሉ መምህራንና ተማሪዎች አጋዥ የሆኑ ሁለት መጽሐፍትን ፅፈዋል፡፡
ፕሮፌሰር ንብረት በተመራማሪነታቸው ከ31 በላይ ጥናቶች በታዋቂና ዓለም ዓቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ ትንተናዎችና ማመሳከሪያዎች ላይ የሚያተኩሩት ጥናቶቻቸው ለዘርፉ ባለሙያዎች ቀዳሚ ማጣቀሻዎች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ንብረት ከማስተማርና ምርምር በተጓዳኝ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተቀብለው በብቃት አገልግለዋል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለዉ የእንሰሳት ሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ በእንሰሳት እርባታ ጣቢያ ሐኪምነት፣ በቬተርናሪ ክሊኒካል ሜድስን ትምህርት ክፍል ኃላፊነት እንዲሁም በድህረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪነት ሰርተዋል፡፡ አዳዲስ ፕሮግራሞችን በማስፋፋትና ያሉትን በማጠናከር ሚናቸው ጉልህ ነው፡፡ ዝቅ ብሎ ሰርቶ ውጤቱን ከፍ ማድረግ ያውቁበታል፡፡ ለአካባቢው ማህበረሰብ አቅማቸው የፈቀደውን ከማድረግ ወደ ኃላ አይሉም፡፡ የተከበሩና ምስጉን ሰው ናቸው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድም ትናንት ግንቦት 22/2012 ዓ.ም በ “Microsoft Teams” ባካሄደው ስብሰባ በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች ተመርመሮ፣ በየኮሌጆቹ አካዳሚክ ጉባዔዎች ተፈትሾ፣ በውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች ተረጋግጦ፣ በዩኒቨርስቲው ሴኔት ታይቶ እና ይሁንታ አግኝቶ የቀረበለትን የዶ/ር ንብረት ሞገስን መረጃ ተመልክቶ ሙሉ ፕሮፌሰር እንዲሆኑ አፅድቋል፡፡
ፕሮፌሰር ንብረት ሞገስ በድጋሜ እንኳን ደስ አለዎት እያልን የአገልግሎት አድማስዎ እንዲሰፋ እንመኛለን፡፡
ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ግንቦት 23/2012 ዓ.ም



