ለጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን በጎ አድራጎት ማህበር ድጋፍ ተደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለጯሂት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምንዱባን በጎ አድራጎት ማህበር ነሐሴ 5/2012ዓ.ም 44 ኩንታል ጤፍና ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች የተሰበሰበ 14,000 (አስራ አራት ሽ) ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

በዕለቱ የጎንደር የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የምእራብ ደንቢያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቸው፣ የዩኒቨርሲቲያችን ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች እና ሌሎች የወረዳው አመራር አካላት ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራም የበጎ አድራጎት ማህበሩን በምን መንገድ በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚቻል አጭር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ልማት ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ካሴ የበጎ አድራጎት ማህበሩን በዘላቂነት ለማቋቋም የወረዳው አስተዳደር፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ሆነው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው እስካሁን እየሰራ ያለው ስራ እንዳለ ሆኖ ያለውን የተማረ የሰው ሀይል በመጠቀም ጥናት በማጥናት፣ ንድፈ ሀሳቦችን በማፍለቅ እና እነዚህን ንድፈ ሀሳቦች ወደ ተግባር በመቀየር የእርዳታ ድርጅቶችን በማፈላለግ ትልልቅ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ አይቸው ወረዳው ወደፊት ሊሰራ የሚገባውን ስራ ካቀረቡ በኋላ፣ ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡ በተጨማሪም ማህበሩን በዘላቂነት ለማቋቋም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡ የማህበሩ የአመራር አካላትም ዩኒቨርሲቲውና የወረዳው አስተዳደር እየሰጡት ያለውን ድጋፍ በዝርዝር በማቅረብ ስለተደረገው ድጋፍ በማህበሩ ስም አመስግነዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ በ2013ዓ/ም ሊሰሩ የሚገቧቸው ያሏቸውን ሀሳቦች ያነሱ ሲሆን፣ የወተት ላሞች እርባታ፣ የንብ እርባታ፣ የእህል ወፍጮ ላይ አተኩሮ ቢሰራ እንዲሁም በቋሚነት የሚታረስ የእርሻ መሬት ወይም የአትክልትና ፍራፍሬ ቦታ የሚሆን መሬት ማግኘት ቢቻል እና ተቋማዊ ሪፎርም ቢደረግ ማህበሩን በዘላቂነት ለመቋቋምና እራሱን ለማስቻል እንደሚረዳ ያላቸውን ሀሳብ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲያችን ከፍተኛ አመራሮች በኩል ለማህበሩ አመራሮች የእህልና የገንዘብ ርክክቡ ተፈፅሟል፡፡



