በጠዳ አካባቢ ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ከ133 መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በተሰበሰበ 23,970 (ሃያ ሶስት ሽ ብር) እንዲሁም በኮሌጁ የተመረተ 23 ኩንታል እህል በጠዳ አካባቢ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 71 የህብረተሰብ ክፍሎች ለሁለተኛ ጊዜ ጳጉሜ 2/2012 ዓ.ም የምግብ እህልና ጥራጥሬ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሃሊ ጀምበሬ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረ/ፕ/ር ዳንኤል ታደሰ፣ የኮሌጁ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ዘርፉ አቡሀይ፣ የጠዳ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ሀይለ እየሱስ መኳንንት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች የተወከሉ አቶ ብሩ አያሌው እንዲሁም ድጋፉን በጉልበታቸውና ጊዜያቸውን መስዋእት በማድረግ ያገዙ የከተማዋ ወጣቶች በተገኙበት ለ71 አቅመ ደካሞች ለእያንዳንዳቸው 30 ኪሎ ግራም ዱቄት እና 14 ኪሎ ግራም ጥራጥሬ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ካህሊ ጀምበሬ፣ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፉ እውን እንዲሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ያስተባበሩትን መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችን እንዲሁም የከተማዋን ወጣቶች አመስግነዋል፡፡ ዶ/ር ካህሊ አያይዘው ከዚህ ዕለታዊ ድጋፍ ባለፈ በቋሚ ስራ ላይ እንደሚያተኩርና አካባቢው በምርት እራሱን ችሎ የተትረፈረፈ ምርት ገቢያ ላይ እንዲገኝ የማድረግ ስራ ከኮሌጁ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተረጅነት ወጥተው ወደፊት በከተማ ግብርና ላይ በመሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ፕሮግራሙን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ወደፊት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቋሚነት ለመደገፍ እና ወጣቶችም እራሳቸውን ችለው ቤተሰባቸውን የሚደግፉ መሆን እንዲችሉ ከቀበሌው አስተዳደር፣ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፕሮጀክት መንደፍ እንደሚገባ ገልጸው፣ ይህንን የተቀደሰ ስራ ላስተባበሩ፣ ሃሳቡን ላፈለቁ በገንዘባቸው እና በጉልበታቸው ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው የድጋፍ እርክክቡ ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡



