በችግር ጊዜ መረዳዳት ባህላችን ነው፡- የማህበረሰብ አገልግሎት በኣፋር ክልል
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሳለፍነው የበጀት ዓመት በርካታ የማህበረሰብ ድጋፎችን በማድረግ ተደራራቢ ችግሮችን ማለፍ ችሏል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት፣ በበሽታው ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ በበሽታው ለተያዙ ግለሰቦችም በቂ የሆነ ህክምናና እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግ እርብርብ አድርጓል፡፡
በተለይም በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበሽታው ተጠቂዎች የሚውል የሕክምና መሳሪያዎች፣ የተለያዮ የምግብ ግብዓቶች ፣ ፍራሽና ከድንበር ወደ ማቆያ ማዕከላት ማመላለሻ አውቶቡስ ድጋፍ ጭምር በመመደብ በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት አቅመ ደካሞችና የቀን ሰራተኞች ለርሃብ የተጋለጡበት ወቅት እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ተወጥቷል፡፡
በቅርቡ ደግሞ በአዋሽ ወንዝ ሙላት በኣፋርና በኦሮሚያ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን በቦታው ተገኝተው ለእያንዳንዳቸው 5 መቶ ሺህ ብር የሚገምት ሳሙናን ጨምሮ የተለያዮ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ መድሃኒቶች፣ አንሶላና ብርድ ልብስ፣ ሩዝና ፓስታ በማከፋፈል ዩኒቨርሲቲው አጋርነቱን ያሳየበት ሥራ ተከናውኗል፡፡



