የአርሶ አደሮች በዓል በመስክ ጉብኝት ተከበረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ስር በሚገኙ የበለሳ፣ የጎርጎራ፣ የዳባትና የሽንታ ምርምር ጣቢያዎች ላይ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የዘር ብዜትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ስራዎች በስፋት እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡ከምርምር ቦታዎቹ አንዱ በሆነው በበለሳ ምርምር ጣቢያ ውጤት የታየባቸው የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ወደ አካባቢው አርሶ አደሮች አንዲወርዱ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም የተዘሩ ሰብሎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው የሚለውን በአካል ለማረጋገጥ፤ አርሶ አደሮችና የዘርፉ ሙያተኞች የተሻለ ልምድ እንዲወስዱባቸው ለማስቻል እንዲሁም ያጋጠሙና የታዩ ችግሮች ካሉ በነሱ ላይ ተወያይቶ የምፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥን ዓላማው ያደረገ የአርሶ አዶሮች የመስክ በዓል ጥቅምት 8/2013 ዓ.ም በምዕ/በለሳ ወረዳ አርባያ ከተማ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡በበዓሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካህሌ ጀምሬ፣ የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጅ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መስፍን፣ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፋንታው፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አንዷለም ሙሉ፣ የምዕራብ በላሳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገድፍ ጌትነት፣ ሎሎች የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ግብርና ሙያተኞች፣ አርሶ አደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዓሉን ታድመዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚያከናውናቸው በርካታ የምርምምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ስራዎች መካከል፣ የአርሶ አደሩን ምርት በማሳደግ ብሎም ቀጣይነት ያለው ለውጥ በግብርናው ዘርፍ ለማበርከት የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች በጥልቀት ማካሄድ፣ ዋነኛውና በስፋት እየጠሰራበት ያለ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፋንታው ገልጸዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በመክፈቻ ንግግራቸው አያይዘውም በአይነትም ሆነ በብዛት የተሻለ ሰብል በበለሳ ምርምር ጣቢያ ድጋፍ አማካኝነት ሊታይ የቻለው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ከአርሶ አደሩ፣ ከወረዳና ከቀበሌ ግብርና ሙያተኞች ጋር ተናቦ በጋራ በመስራት ነው ብለዋል፡፡ መሰል ስራዎች ተጠናክረው በስፋት እንደሚሰሩም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የዘር ድጋፍ በክላስተር (በኩታ-ገጠም) ተዘርቶ አሁን በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ የሽምብራ ማሳ፣ የአካባቢው ተወላጅ በሆኑ ባለሀብት (በአቶ አማረ አለሙ) የተሰሩ ከግብርና ጋር የተያያዙ የልማት ስራዎች፣ እንዲሁም አርባያ በለሳ በሚገኘው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርመር ጣቢያ ላይ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ተዘርተው አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰብሎች (የሽምብራ፣ የማሽላ፣ የጤፍ፣ የቦሌቆና የማሾ ሰብሎች) በበዓሉ ተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡ ጉብኙቱን መሰረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል፤ የተሻሉ እሚባሉ የመፍትሄ ሀሳቦችና የወደፊት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡በጉብኝቱ ወቅት ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ውባለም አበባና አቶ አዝኖልኝ ባይለየኝ ይገኙበታል፡፡ አርሶ አደሮቹ በዩኒቨርሲቲው ስለተደረገላቸው የዘር ድጋፍ ከልብ አመስግንዋል፤ ምርትና ምርታማነትን ለመሳደግ በጋራ የሚለሙ ሰብሎችን በኩታ ገጠም ማልማት የተሸለ ውጤት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት 9/2013 ዓ.ም




