የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ10ዓመት ረቂቅ መሪ ዕቅድ ውይይት ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ2008- 2012ዓ/ም በታቀደው ስትራቴጅክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ10ዓመት መሪ ዕቅድ (ከ2013 – 2022) ላይ ህዳር 17/2013 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት በአልሙኒየም ህንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም ከ2008- 2012ዓ/ም የነበረው የስትራቴጅክ እቅድ ስኬታማ እንደነበር አውስተው፣ ምንም እንኳ ያለፈው ዓመት ብዙ አካባቢያዊና ሀገራዊ ችግሮች የታለፉበት ቢሆንም ተቋሙ በችግር ውስጥም ሆኖ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡ፣ ከስመ-ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እንዲውል እና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቅቷል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አሥራት አያይዘውም በቀጣይ አስር ዓመታት ሊሰሩ የታሰቡ ሥራዎች በሀገር ደረጃ በተሰጠው መሪ እቅድ እና በዮኒቨርሲቲያችን ተልዕኮ እና ልየታ መሠረት የስትራቴጅክ ረቂቅ እቅድ ተዘጋጅቶ መቅረቡን ገልፀው በረቂቅ እቅዱ ላይ ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግና ግብዓት በመስጠት ሊተገብር የሚችል እቅድ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ያገኘናቸው ልምዶች እና የስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ውጤቶች ለቀጣይ አስር አመታት የልማት መሪ እቅድ በግብዓትነት መዋል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠልም በፕላንና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ጋሻው ነበሩ ከ2008 – 2012ዓ/ም ስትራቴጅክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ሪፖርት እና የ10ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ (ከ2013-2022) የቀረበ ሲሆን፣ በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ በተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው በእቅድ ገምጋሚ ኮሚቴ አባላት ምላሽ የተሰጠበትና ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ውይይቱ ሕዳር 18/2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ ******************************************************
ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 18/2013ዓ/ም






