የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ትውውቅ መርሀ-ግብር ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ2013ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገብረው የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት፣ ለአጋርና ባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ እና ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር መጋቢት 14/2013ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በመርሀ-ግብሩ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሞላ መልካሙ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፣ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የካውንስል አባላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

መርሀ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ቢሆንም በተጠናቀቀው የስትራቴጅክ ዘመን በመማር ማስተማሩ፣ በምርምሩ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጅ ሽግግር ተግባራት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል፡፡ ለአብነትም የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት መተግበር፣ ዩኒቨርሲቲው ለተከታታይ 3 አመታት በኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት እና ትምህርት ሚኒስቴር የ1ኛ ደረጃ ዋንጫ ተሸላሚ መሆን እንዲሁም ከ9ሺህ በላይ ሰራተኞችን የስራ ምዘና ድልድል የጎላ ቅሬታ ሳይታይበት መሰራቱም ከስኬቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡ ለዚህ ስኬት መመዝገብም አስተዋፅኦ ለነበራቸውን አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአስር አመቱ መሪ እቅድ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፕላንና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይክተር በአቶ ጋሻው ነበሩ እና የስትራቴጅክ እቅድ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በሆኑት በወ/ሮ ፀጋ ሀጎስ አማካኝነት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይህ መሪ እቅድ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ተመርምሮ በየደረጃው በስራ አመራር ቦርድ ከተገመገመ በኋላ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቀርቦ የተሰጡ አስተያየቶችን በማካተት ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል የተላከ ነው፡፡
በመጨረሻም የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱን ለማስተግበር እና ለመተግበር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በወ/ሮ ብዙሀን ጌትነት አማካኝነት የቃለ ማህላ ስነ-ስርዓት ተካሂዶ እና ለስትራቴጅክ እቅድ ዝግጅት ኮሚቴ አባላት የምስጋና የሽልማት ወረቀት ተበርክቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በስራ ፈጠራ ባህል የተቃኙ ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ችግር ፈች ምርምር እና አሳታፊ የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠትን ተልእኮ በማንገብና በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ 10 ቀዳሚ የምርምር የኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ሆኖ የማየትን ራዕይ በመሰነቅ በዚህ መርሀ ግብር ጉዞውን አንድ ብሏል፡፡



