በከብት ማድለብ ስራ ላይ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና እየተሰጠ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን በወገራና በአርጫሆ ወረዳዎች በከብት ማድለብ ስራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶችና ወጣቶች በስራ ፈጠራ፣ በንግድ ስራ አመራር እንዲሁም በእሴት ሰንሰለት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈተቱት የኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር አንዋር ኑሩ ናቸው፡፡ ዶ/ር አንዋር ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አውስተው፣ ወደፊት መሰል የምርምር ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግራዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ለተሳተፉ የኮሌጁ አባላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡

በማድለብ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሳይንሳዊ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ በማስቻል፣ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግና ምርታማነታቸውን መጨመር የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መ/ርት እመቤት ነገሰ ተናግረዋል፡፡ የማድለብ ስራው ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርጉ ምክንያቶች፣ የስራ ፈጠራና አማራጭ የኑሮ ዘዴ፣ የንግድ ስራ አማራር ጥበብ፣ የመኖ አያያዝና አጠቃቀም የሚሉትና የመሳሳሉት በስልጠናው በስፋት የሚብራሩ ሀሳቦች መሆናቸውን አስተባባሪዋ አያይዘው ገልጸውልናል፡፡

በሌሎች ወረዳዎች ለሚገኙ አድላቢዎችና ለዘርፉ ሙያተኞች መሰል ስልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ እንደተያዘ ከመ/ርት እመቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህ ስልጠና ነገ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን በመጪው ሀሙስና አርብ (መጋቢት 23 እና 24/2013 ዓ.ም) በቆላድባ ከተማ የሚሰጥ የይሆናል፡፡





