ለፊዚክስ ትምህርት እገዛ የሚያደርጉ ቁሳቁሶች በድጋፍ መልክ ሊሰጥ ነው፤ ለዘርፉ መምህራንም ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው ፊዚክስ ት/ት ክፍል ከዚህ በፊት በጎንደርና አካባቢው ለሚገኙ ት/ቤቶች ለተግባርና ለሙከራ ትምህርት ግልጋሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በድጋፍ መልክ ማበርከቱንና የዘርፉ መምህራንም እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ትምህርት ክፍሉ ለዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ት/ት ቤት እንዲሁም ለካቢታና ለመተማ ዮሀንስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የቤተ-ሙከራ እቃዎችን በድጋፍ መልክ ለማበርከት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በመሆኑም ከየትምህርትበቶቹ የመጡ የፊዝክስ መምህራን የቤተ ሙከራ ዕቃዎቹን ቅድሚያ እንዲያውቋቸውና እንዲገነዘቧቸው የሚያስችል ስልጠናዎችን በት/ት ክፍሉ የላቦራቶሪ ክፍሎች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በመርሀ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው የጠፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ጌትነት ማስረሻ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር ብርቁ ደመወዝ መርሀ ግብሩን በንግግር አስጀምረዋል፡፡

ከስልጠናው በኋላ ለየትምህርትቤቶቹ ለሙከራና ለተግባር ትምህርት የሚያገለግሉ 72 (ሰባ ሁለት) ቁሳቁሶች በድጋፍ መልክ የሚሰጡ ሲሆን በነዚህም ቁሳቁሶች ከ 30(ሰለሳ) በላይ ለሚሆኑ የተግባር ትምህርትና ዕይታ መስጫ (Demonstration) ሙከራዎች ራሳቸውን ችለው የሚከናወንባቸው እንደሆነ ከትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ከዶ/ር ተሸገር አክሌ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ ስልጠና አርብ መጋቢት 24/2013 ዓ.ም የቤተ ሙከራ ቁሳቁሳች ርክክብ ከተከናወነ በኋላ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡



