ስርአተ-ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት በሚል ርእስ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የስርአተ-ፆታና ልማት ትምህርት ክፍል ለደባርቅ ወረዳ የባለድርሻ አካላት ስርአተ-ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከልና ምላሽ መስጠት በሚል ርእስ ዙሪያ የባለ ድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ አላማ ያደረገ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና መጋቢት 23 እና 24/2013ዓ/ም በደባርቅ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር መስፍን ደስዬ ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ ስርአተ-ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በጣም ዘርፈ ብዙ እየሆነና ቅርፁን እየቀያየረ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለ እንደሆነ፣ በዋናነት ሴቶችንና ህጻናትን የሚጎዳ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችንም የሚያካትት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የባለ ድርሻ አካላትንና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደ አንድ ችግሩን ለመከላከልና ለመፍታት የሚያገለግል መሳሪያ እንደሚታሰብ ዶ/ር መስፍን አክለው ገልፀዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በስርአተ-ፆታ ምንነትና ጽንሰ ሃሳብ፣ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምንነትና አይነቶች፣ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት መንስኤዎችና ምክኒያቶች፣ የሚያስከትለው ችግሮችና ጉዳቶች፣ የመከላከያ ሂደቶችና ህጋዊ ማእቀፎች በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ በፕሮጀክቱ አባል መምህራን ገለፃ ተደርጎባቸዋል፡፡ በቀጣይ ጊዚያት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት በዘዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም የትምህርት ክፍሉ መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አለሜነህ ጌታነህ ይህንን ችግር ለመፍታት የመንግስት ተቋማት ከማህበረሰቡ እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመስራት የሴቶችንና የህፃናትን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ ሆነው መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡




