ከቋራ – መቅደላ የማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝም እና የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የምክክር መድረክ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በንጋት ኢንተግሬትድ ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን አዘጋጅነት ከቋራ-መቅደላ የማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝም እና የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የምክክር መድረክ ሚያዚያ 4/2013 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አልሙኒየም አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በዝግጅቱ የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት ዓፀደወይን ፣ ም/ፕሬዝዳንቶች፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች ፣የአብክመ ዋና አማካሪ አቶ መርሃፅድቅ መኮነን፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢና የደ/ማርቆስ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ፣ የንጋት ኢንተግሬትድ ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀጋ ዓለሙ፣ ከአማራ ክልል ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ፕሬዝዳንቶች፣ ከፍተኛ አመራሮች እና የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

“በቅድሚያ እንኳን ወደ ሰላሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ጥንታዊና ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በሰላም መጣችሁ በማለት ዩኒቨርሲቲያችን ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶች መካከል የቱሪዝም ሀብት ልማትን ማጠናከር፣ የቅርስ እንክብካቤን መደገፍ፣ ቅርሶቻችንና ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋዎቅ፤ በተለያዩ ጊዜያት የተዘረፉ ቅርሶቻችን እንዲመለሱ የበኩላችን ጥረት በማድረግና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን መጨመር ይገኙበታል” በማለት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡
የስራ ፈጠራ ባህልን ማሳደግ፣ ታሪክ የተሰራባቸውን ቦታዎች መጠበቅ እና ከቋራ እስከ መቅደላ ያሉ ቦታዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ማስቻል የውይይቱ ዋና አላማ እንደሆነ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ግርማ ታያቸው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ተበታትና የነበረችውን ኢትዮጵያን በአንድ ማእከላዊ መንግስት በመመስረት ህዝቦቿ የስልጣኔ ተቋዳሽ እንዲሆኑና ሃገሪቱን ማዘመን የአፄ ቴወድሮስ ራእይ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በመጨረሻም ስለወደፊቱ ከቋራ-መቅደላ የፕሮጀክት አካሄድ፣ ተፈፃሚነት እና ቀጣይነት ላይ አጠቃላይ ውይይት እንዲሁም ኮሚቴዎችን የማዋቀር ስራ ተሰርቶ መድረኩ ተጠናቋል፡፡



