በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ ተካሄደ
የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት በአፍሪካ በአንደኛነት ደረጃ በዓለም አቀፍ ደግሞ በ8ኛ ደረጃ የተቀመጠው የታላቁ የህዳሴ ግድብ በ2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግድቡ 6000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ከ80% በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አሁን ላለባቸው የኤሌክትሪክ ሀይል እጦት መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመሆኑም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚመክር 9ኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የውሀ ህግ፣ ሉአላዊነትና የግጭት አፈታት በሚል በጎንደር ዩኒቨርሰቲ ህግ ትምህርት ቤት አዘጋጅነትና እና በጎንደር ዩኒቨርሰቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከግንቦት 03 እስከ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም በጎሀ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ፣ የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር አብርሀ አዱኛ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ጀንራል ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተ/ከንቲባና የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ሞላ መልካሙ፣ ሌሎች የሚመለከተቸው የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባኤው ተሳትፈዋል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ ያስታወሱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ግድቡ የሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም የህዝቦቿን ብሎም የጎረቤት ሀገር ህዝቦች ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ምሁራን የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት እንዲኖር ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚገኝ ዶ/ር አስራት በንግግራቸው አያይዘው አንስተዋል፡፡ በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሱዳን ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ፣ በኢትዮ-ሱዳን በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በህገወጥ ንግድና የሰዎች ዝውውር በስነ-ህዝብ፣ በትምህርትና በመሳሰሉ ጉዳዮች በአጋርነት እየሰራ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን የነጻነትና የሉአላዊነት ጉዳይ እንደሆነ በአብይ ንግግራቸው ወቅት የተናገሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ (የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል) የሀገራችንን ሉአላዊነትና ነጻነት ለማስከበር ደግሞ ሁሉም ዜጋ ለሀገር አንድነት፣ አብሮነትና ለሰላም በመጀመሪያ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ የህዳሴ ግድብና ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታን፣ የህዳሴ ግድብ የውሀ አያያዝ፣ አጠባበቅንና ስምምነትን፣ የኢትዮ-ግብጽ የጎንዮሽ ግንኙነትንና የመሳሳሉትን የሚመለከቱ ጹሁፎች በምሁራን ቀርበዋል፡፡ የቀረቡትን ወረቀቶች መሰረት በማድረግ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፤ የወደፊት አቅጣጫ ተቀምጦ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የጉባኤው ተሳታፊዎች ዛሬ ሰኔ 4/2013 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ግቢዎች በማከናወን የአረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠው መርሀ ግብሩ ተጠናቋል፡፡




