የኢትዮ-ሱዳንን ታሪካዊ ዳራና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የተመለከተ አውደ-ጥናት ተካሄደ
ድንበር/ወሰን የሉዐላዊ ሀገር ክልላዊ መስመር ከመሆኑ ባሻገር የአንድ ሀገር ህዝቦች በዜግነት እሚካተቱባትና ያለ ገደብ እሚንቀሳቀሱበት መስመር ነው፤ ድንበር የአንድ ሀገር መንግስት ህዝቡን በኃላፊነት የሚመራበትና የሚያስተዳድርበት ዓለም አቀፍ መስመር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያና ሱዳን ከ 1600 ኪ.ሜ በላይ የሚጋሩት ወሰን ቢኖራቸውም እስከ አሁን ይህ ነው የሚባልና በህግ ተለይቶ የሚታወቅ የወሰን ክልል ሳይኖራቸው ለረዥም ዓመታት መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ክፍተት ለመሙላት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥናትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ሀገራዊ ውይይቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአንጋፋው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በፕ/ር ሙላቱ ውብነህ “የኢትዮ ሱዳን ወሰን ታሪካዊ ሂደቱና አለመካለሉ ለፈጠራቸው ችግሮች የመፍትሄ ሀሳቦች” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ታሪካዊ መጽሀፍ ዩኒቨርሲቲው ስፖንሰር በማድርግና ለህትመት ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የሁለቱ ሀገር ህዝቦች ያላቸውን ቅድመ-ታሪካዊና ታሪካዊ ግንኙነቶች በማጠናከር እንደ ጎረቤት ሀገር የሚያጋጥሟቸውን አለመግባባቶች በሰለም እንዲፈቱ የሚያስችል አውደ – ጥናት ዛሬ የካቲት 9/2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዴንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አማራሮች፣ የማህበራዊና ስነ ሰብዕ ኮሌጅ መምህራን፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ውይይቱን ታድመዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምነቱና ከጎረቤት ሀገር ሱዳን በቅርብ ርቀት እንደ መገኘቱ መጠን ከሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትምህርት፣ በህገ- ወጥ ሰዎች ዝውውር፣ በአባይ ጉዳይና በሌሎች መስኮች በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ በመክፈቻ ንግግራቸው የገለጹት ዶ/ር አስራት፣ ትምህርትን በተመለከተ የሱዳን ምሁራን የአረበኛ ቋንቋን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማስተማር፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአንጻሩ የአማርኛ ቋንቋን ለሱዳን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለማስተማር የትምህርት ካሪኩለም ተቀርጾ ወደ ተግባር ሊገባ እንደ ሆነ ለአብነት አንስተዋል፡፡ ሀገራቱ አዋሳኝ ድንበሮቻቸውን መሰረት በማድረግ የሚታየውን አለመግባባት በአጭር ጊዜ ለመፍታትና በጋራ እንዲበለጽጉ ለማስቻል፣ ሳይንስና ታሪክን መሰረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮች በዘርፉ ምሁራን መካሄድ እንዳለባቸውና ቀጣይነት ያላቸው ሀገራዊ ውይይቶች (National Dialogues) መደረግ እንዳለባቸው አያይዘው አሳስበዋል፡፡

“የአውሮፓና የአፍሪካ ምሁራን በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ስላለው አርኪዮሎጂአዊ ግኝቶች ያላቸውን ሀሳብ በማየት፣ የሀገራቱን (የኢትዮጵያና የሱዳንን) ትክክለኛ ታሪክና ቅድመ ታሪክ በመመርመር አዲስ የወሰን ግንዛቤ መያዝ (Drawing a New Line Between History and Pre-history፡ A Debate between The European Historians’ and the African History Based on the Archaeological Discoveries in Ethiopia and Sudan)” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ሱዳን ሀገር ከሚገኘው ከሱዳን ዩኒቨርሲቲ በመጡት አንጋፋ የታሪክ ምሁር በዶ/ር ኦማር አል አሚን በገለጻ ቀርቧል፤ ስለ “ኢትዮ-ሱዳን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት (People to People Relations Between Ethiopia and Sudan)” በአንጋፋው የሶሺዮሎጂ ምሁር በዶ/ር ቡሻ ታአ ቀርቧል፡፡

የቀረቡትን ገለጻዎች መሰረት በማድረግ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ የሱዳንና የኢትዮጵያ የባህላቸውና የሰዎቻቸው መመሳሰል እንዲሁም ጉርብትናና የረዥም ጊዜ የታሪክ ቁርኝት በፖለቲካ ጥበብ የተገኘ አለመሆኑ፣ ይልቁንም በተፈጥሮ ጥበብ የተገኘ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል፡፡ ጥቂት የፖለቲካ ሴረኞች የሁለቱን ሀገራት ህዝብ ወደአልተፈለገ ግጭት ውስጥ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች በተለይም በሱዳን በኩል ሰሞኑን መታየቱ በውይይቱ ተገልጿል፤ በመሆኑም ምሁራኑ ችግሩን በሚገባ በመመርመርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀጣይነት ባለውና በሰከነ መልኩ በመወያየት የጥፋት ኃይሎችን ሴራ በቶሎ ማክሸፍ እንደሚገባ ከመድረኩ በስፋት ተነስቷል፡፡
በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ የአውደ ጥናቱን አስፈላጊነት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ውይይቱ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ከሱዳን ድረስ መተው ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ (ለዘርፉ ምሁራን) ላካፈሉት ለዶ/ር ኦማር ያላቸውን ልባዊ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡



