ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ከጥናትና ምርምር ጽንሰ-ሀሳቦች ጋር የተያያዙ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለዩኒቨርሲቲው ድህረ ምረቃ ተማሪዎች (ለ2ኛና 3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች) ከየካቲት 17-18/2013ዓ/ም ሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ጌትነት ማስረሻ ለሰልጣኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፤ በማሰልጠንም የተሳተፉ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ድሀረ ምረቃ ፕሮጋራሞች ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዶ/ር ብስራት በበኩላቸው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ችግር ፈች ምርምሮችን በማካሄድና የምርምር ውጤቶችን በታወቁ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ለማሳተምና ተደራሽ ለማድረግ፣ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከምርምር ጋር የተያያዙ ሳይንሳዊ ሀሳቦችን ማወቅና መተግበር እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ብስራት በመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል፡፡
የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛል አጻጻፍ፣ የማኑስክርቢትና የሰሚናር አጻጻፍ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስነ ዘዴዎችና የተያያዙ ጉዳዮች ስልጠናው ትኩረት የሚሰጥባቸው ነጥቦች እንደሆኑ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ድህረ ምረቃ አስተባባሪ ከሆኑት ከዶ/ር አጥናፉ ጓዴ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡




