የጎርጎራ ከተማ መሪ እቅድ ዝግጅት የደረሰበት ደረጃን የተመለከተ ውይይት ተካሄደ
የጎርጎራ ከተማን መሪ እቅድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዲሰራ ሃላፊነት መሰጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ የመሪ እቅድ ዝግጅቱ የደረሰበትን ደረጃ መሰረት ያደረገ ውይይት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኒክ ቡድን አባላትና የባህርዳር ከተማን መሪ እቅድ ባዘጋጀው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኒክ ቡድን መካከል ዛሬ የካቲት 27/2013 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የገበታ ለሃገር እቅድ ዝግጅት ላይ ሙያዊ አበርክቶ ከማድረጉ ባለፈ የጎርጎራ ከተማን መሪ እቅድ ለማዘጋጀት የቴክኒክ ቡድን አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ የእቅድ ዝግጅት ቡድን የወደፊቷን ትልቋንና ዉብ የሆነችው የጎርጎራ ከተማ በእቅድ ተመርታ ከታሰበው እንድትደርስ ለማድረግ ከጎርጎራ እስከ አብርጃሃ ያለውን አካባቢ ለይቶ ለእቅድ ዝግጅቱ መረጃዎችን ከመሰበሰብ ጀምሮ መሪ እቅዱን የማዘጋጀት ስራ እየሰራ ነው፡፡
ለነዋሪዎቿና ለአካባቢው ማህበረሰብ ምቹ የሆነችና የዘመናት የልማት ጥያቄያቸውን የምትመልስ ታሪሃዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ይዘቷን በጠበቀች መልኩ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችውን ጎርጎራን ለማምጣት መሪ እቅዷን በተለየ እይታ ማየትና ሌሎች ከተሞች ላይ ከተሰሩ ስራዎች ከተፈጠሩ ችግሮች መማርና ተሞክሮዎችን ወስዶ መሰል ችግሮች ጎርጎራም ላይ እንዳይከሰቱ ልምዶችን እየቀመሩ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡
በመሆኑም የጎርጎራ እቅድ ዝግጅት የደረሰበት ደረጃ መነሻ በማድረግ የቡድኑ አባላት የባህርዳር ከተማ መሪ እቅድ ካዘጋጀው ቡድን ጋር ሰፊ ውይይትና በቀጣይ ያሉ ስራዎችን ሂደት በተመለከተ የምክክር እና የልምድ ልውውጥ ስራ ተካሂዷል፡፡ የጎርጎራ እቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ አየልኝ ተበጀ በውይይት መድረኩ ወደ ፊት ሊገጥሙ የሚችሉ ጉዳዮችንና መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ሊያሳይ የሚችል በርካታ ልምዶችን የቡድናቸው አባላት እንዳገኙበት የገለጹ ሲሆን በሌላ መኩል የባህርዳሩ እቅድ አዘጋጅ ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር መንግስቴ አባተ በበኩላቸው የጎርጎራ ከተማ መሪ እቅድ አዘጋጅ ቡድን ጥሩ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸው ወደ ፊትም ተመካከሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አጠቃለይ ስራውን እየተከታተለው ያለው እና ይህንን የምክክር መድረክ ያዘጋጀው የማህበረሰብ አገለግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆነው አቶ ሰለሞን ፈንታው በበኩሉ ውይይቱ እጅግ ፍሬያማና ችግሮች ከመለሰታቸው በፊት ቀድሞ የሌሎችን ልምድ ወስዶ መስራት ተገቢ እንደሆነና መሪ እቅዱን በጥራት ለመስራት ትልቅ ፋይዳ የነበረው ውይይት እንደሆነና ለስራው ጥራት ሲባል በተለይ ውበቷና ሳንባዋ የሆነውን ጣናን የማትጎዳ ጎርጎራን ከመፍጠር አንጻር እንደዚህ አይነት የውይይቶች መድረኮች ወደፊት እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
ስራዉን በበላይነት እየተከታተሉት ያሉት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕረዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ለሁለቱም የቡድን አባላት ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበው የሚሰራውን እቅድ ጥራት ከማስጠበቅ ባለፈ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እብዲጠናቀቅ ባለሙያዎች ይህንን ታሪካዊ ሃላፊነት በትጋት መስራት እንደሚጠበቅ እንዲሁም ተመሳሳይ መድረኮችን እንደአስፈላጊነቱ ልምድ ወደ አላቸው ቦታዎች በመሄድ ወይም ልምድ ያላቸውን በማምጣት የበለጠ ጥራቱን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ የነገዋን ጎርጎራ ለማምጣት ዛሬ ላይ ጥሩ እቅድ ከማዘጋጀት እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡




