“በአለማችን 340 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞች በስራ ላይ የተለያዩ አደጋዎች ይደርስባቸዋል!” አቶ ተስፋየ ሐምቢሳ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአካባቢና ሙያ ደህንነትና ጤና አጠባበቅ ት/ክፍል በጎንደር ከተማ ህንጻ ግንባታ ስራ ፕሮጀክቶች የሙያ ደህንነትን በማሻሻል የስራ ላይ አደጋዎችን ለመቀነስ አላማ ያደረገ ስልጠና መጋቢት 4ና 5/2013 ዓ.ም ተሰጠ፡፡ በስልጠናው የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ወ/ሪት ቤተልሄም አንተነህን ጨምሮ በህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞችና ተቋራጮች፣ የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኞችና ኃላፊዎች፣ የሙያ ደህንነትና ጤና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ተስፋየ ሀምቢሳ የአለም ስራ ድርጅት ዘገባን ዋቢ በማድረግ “በአለማችን 340 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰራተኞች በስራ ላይ የተለያዩ አደጋዎች ይደርስባቸዋል!” ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 2.3 ሚሊዮን ከስራ ጋር ተያያዥነት በአላቸው አደጋዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ አብራርተዋል፡፡ አደጋዎች ከሚከሰቱባቸው አካባቢዎችም ዋነኞቹ የግንባታ ስራዎች መሆናቸውን ገልጸው ከ6 አደጋዎች አንዱ በግንባታ ስራ ላይ የሚከሰት አደጋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ዋናው ምክንያት በግንባታ የሚሰማሩ ሰራተኞች በብዛት ወጣቶች መሆናቸውና ስለ አደጋ ቅድመ መከላከል በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ የግንባታ ስራ በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ተስፋየ፣ ከስራው ጋር የተያያዙ የስራ ላይ አደጋዎችን ስለመከላከል ያለው ግንዛቤና ጥንቃቄ ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም ስልጠናው መሰጠቱ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት መሰል አደጋዎችን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስተባባሪው አክለው ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው የተሰጠው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአካባቢና ሙያ ደህንነትና ጤና አጠባበቅ ት/ክፍል መምህራን በአቶ ተስፋየ ሐምቢሳ፣ዳዊት ጌታቸውና አውራጃው ደሴ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዋና ሀሳቦችም የሙያ ደህንነትና ጤና፣የሙያ አደጋዎች፣ ጠንቆችና መከላከያቸው የሚሉ ናቸው፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች በማካፈልና አደጋዎችን በመከላከል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ይጠበቃል፡:



