የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለ ‘ንድፍት’ በሽታ መድሀኒት ማግኘታቸውን ገለጹ
ባደጉት ሀገራት ከእንስሳት መብት ጋር በተያያዘ በመንግስት ደረጃ የተለያዩ ህግጋቶች የጸደቁ በመሆናቸውና የተለያዩ የእንስሳት መብት ተከራካሪ ድርጅቶች በመኖራቸው፣ የየሀገራቱ ዜጎች እንሰሶችን ማንገላታት፣ ጉልበታቸው ያለአግባብ መበዝበዝና የመሳሰሉ በደሎችን በእንስሳት ላይ ማድረስ ፈጽሞ አይችሉም፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ጉዳይ በሀገራችን አውድ ስናየው ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡
በተለይም በከተሞች አካባቢ የጋሪ ፈረሶች ላይ የሚደርሰው የስራ ጫናና የመሳሳሉ በደሎች የከፉ ናቸው፡፡ በነዚህ ከፍተኛ የሆኑ በደሎች የተነሳ ፈረሶቹ ለተለያዩ በሽታዎች በተለይም ‘ንድፍት’ ለተባለው ገዳይ በሽታ ይጋለጣሉ፡፡ ስለሆነም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና ተመራማሪዎች ለዚህ ክፉ በሽታ አይነተኛ መፍትሄ በምርምር ማግኘታቸውን ለማብሰር መጋቢት 4/2013 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡

የሀገር በቀል እጽዋትን በመጠቀም የተቀመመው ይህ መድሀኒት፣ የጋማ ከብቶችን (በተለይም የጋሪ ፈረሶችን) በማጥቃት የሚታወቀውን ኢፐዘዋቲክ ሊምፋንጂቲስ/Epizootic lymphangitis) ወይም በተለምዶ ‘ንድፍት’ እየተባለ የሚጠራውን በሽታ ከስልሳ አምስት በመቶ በላይ ለመከላከል የሚያስችል ውጤት ላይ የደረሰ መሆኑን የገለጹት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ቴዎድሮስ ፋንታሁን፣ በቀጠይ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ለምርምር ቡድኑ ድጋፍ ካደረጉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡

በደ/ታቦርና በጎንደር የሚገኙ የጋሪ ማህበራት ተጠሪዎችና ባለንብረቶች፣ የእንስሳት ጤና ሙያተኞች ስለተገኘው መድሀኒት አጠቃቀምና ተያያዥ ጉዳዮች በተመራማሪዎች የተደረገውን ገለጻ ተከታትለዋል፡፡ ገለጻውን መነሻ በማድረግም በፕ/ር መርሻ ጫኔ መሪነት የሙሉ ቀን ውይይት አድርገዋል፡፡ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

ከአነጋገርናቸው ተሳታፊዎች መካከል ከጎንደር ከተማ የመጡት የጃንተከል ጋሪ ባለ ንብረቶች ማሀበር ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ አዱኛ ስዩም ይገኙበታል፡፡ አቶ አዱኛ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራራማሪዎች ለጋማ ከብቶቻቸው ጠንቅ ለሆነው ገዳይ በሽታ መፍትሄ በማግኘታቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የተገኘውን መድሀኒት በአጭር ጊዜ በብዛት ተመርቶ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በስፋት እንዲሰራጭ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡



