የአዕምሮ ጤናን በትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሳወቅ የሚያግዝ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ለጎንደር ከተማ ፈለገ አብዮት 1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ የትምህርት ቤት ነርሶች (school nurses) እና ስነ-ልቦና አማካሪዎች የአዕምሮ ጤናን በትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሳደግ የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከየካቲት 10-12/2013 ተሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር መስፍን ደስየ ጤናማ የሆነ የትምህርት ስርዓት እንዲኖር ከተፈለገ በታዳጊ ተማሪዎች ዘንድ የአእምሮ ጤና ስልጠና ግንዛቤ እንዲኖር ማስቻል ለወደፊት ህይወታቸው አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የአዕምሮ ጤናና የሰነ-ባህሪ ችግሮች ብዙ ጊዜ የሚከሰቱት በ 1ኛ ደረጃና ወጣት እድሜ ላይ ባሉ ታዳጊ ልጆች እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ በማለት የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ትራጥ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፕ/ር የማታው ወንዴ ናቸው፡፡ “ልጆች ከወላጆቻቸው ይልቅ በት/ት ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፤ በመሆኑም መምህራኑ ስለአዕምሮ ጤና እውቅና በበቂ ሁኔታ እንዲኖራቸው ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡” በማለት ፕ/ር የማታው አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል መምህር ተስፋየ ታደለ በበኩላቸው፣ በሁለት የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የጥናት ውጤት ላይ በመነሳት ለወደፊት መሰል ስልጠናዎችን ለሌሎች 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት ቅድመ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡



