
የአርሶ-አደሩን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልን ዓላማ ያደረገ አዲስ ፕሮጀክት ወደ ስራ ገባ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ ሪሳ (RISA: Research and Innovation Systems in Africa) እና ከዩኬ ኤድ (UKAID: from the British People) ከተሰኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ፣ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ “አዳዲስ ከግብርና ምርምር የወጡ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት የአርሶ አደሩን (በተለይም የሴት አርሶ-አደሮችንና የኢኮኖሚ ውስንነት ያለባቸውንና የ አካል ጉዳተኛ አርሶ አደሮችንም) የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልን ዓለማው ያደገ ፕሮጀክት” ወደ ስራ መግባቱን በማስመክት የመክፈቻና የትውውቅ መርሀ ግብር ዛሬ የካቲት 07/2015 ዓ.ም በማራኪ ግቢ አሉሙንየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የዩኒቨርሲቲያችን የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግገር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የአማራ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ፣ ሌሌች የዩኒቨርሰቲያችን ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌ የመጡ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻ አካላት በመርሀ- ግብሩ ተሳትፈዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ያስታወሱት ዶ/ር ቢኒያም ዩኒቨርሰቲው የመመህራንን የመመራመር አቅም ይበልጥ እንዲሳድጉ ለማስቻል በተለያዩ ጊዚያት ልዩ ልዩ የስራ ላይ ስልጠናዎችን በመስጠቱ፣ መምህራኑ በምርምር ተግባራት በኩል ውጤታማ ሊሆኑ እንደቻሉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚዳንት ዶር አስራት በበኩላቸው መርሀ ግብሩን በመክፈቻ ንግግግራቸው ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሰቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና በሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ተቋማዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆያቷል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሰቲው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት አጋሮችን ተሳትፎ በማሳደግ የተቋሙን የምርመር ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ እንደመጣ አያይዘው ተናግረዋል፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ የሆኑ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማሸነፍ የማህበረሰባቸውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየተጉ ለሚገኙት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ፕሬዚዳንቱ በተቋማቸው ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡

ስለ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ መረጃ በአቶ ከፍያለ እንየው (የፕሮጀክቱ ማኔጀር)፣ የግብርና ቴክኖሎጅዎችን እንዴት ማዘመንና ማሻሻል እንደሚቻልና ተያያዥ ጉዳዮች በዶ/ር ፍስሀ ዘገየ (ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት)፣ እንዲሁም ስለ ባለድርሻ አካላት ሚናና ኃላፊነት በአቶ ዳንኤል ንጉሴ (በፕሮጀክቱ ም/ ዳይሬክተር) ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎች እንደየ ቅደም ተከተላቸው ቀርበዋል፡፡ የቀረቡትን ጽሁፎች መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ይበጃሉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦችና የወደፊት አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለጊዜው ለአንድ ዓመት እቅድ እንደተያዘለት እና በጥናት የለያቸው በጎንደር ዙሪያ የሚገኙ ቀበሌዎችም ሰንደባና ምንጥራ ሲሆኑ፣ ተግባረዊ በሚሆነው በዚህ ፕሮጀክት በድምሩ የ 150 አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ታስቦ ወደ ስራ እንደተገባ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በጥናትና ምርምር የተደገፉ የንብ ኃብት ልማት፣ የአቦካዶ አትክልት ምርትና የሩዝ ምርት ደግሞ አርሶ አደሮቹ በፕሮጀክቱ ድጋፍ በዋናነት የሚሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች እንደሆኑ ከውይይቱ ለመረዳት ችለናል፡፡



