ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸው ተገለፀ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዳጠናቀቀ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን መስከረም 7/2012 ዓ.ም ገለፁ፡፡ፕሬዚዳንቱ ግብአት የማሟላት ስራ ማለትም፣ የመምህራን ቅጥርና ቁሳቁስ የማሟላት ስራ መሰራቱን፣ በዩኒቨርሲቲው የተለመደውን ለመምህራን የኢንዳክሽን ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የሚቀበለው የተማሪ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የተማሪዎች የመኝታ ክፍል ጥገና፣ የቀለም ቅብ እና የማጽዳት ስራ መሰራቱን፣ የምግብ ግብአት አቅራቢዎችን የመለየት ስራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መተግበርን በተመለከተም ግንዛቤ የመፍጠር እና ለአንደኛ አመት ተማሪዎች የመምህራንና የመጻሕፍት ዝግጅት ስራ እንደተሰራ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በዩኒቨርሲቲው ፈንድ የሚደረጉትን የመለየት ስራ መሰራቱን በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የጥራት ተሸላሚ በመሆኑ ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ለመቀመር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተላከ ቡድን ምርጥ ተሞክሮውን ለመቀመርና ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋት ስራ ሲሰራ መቆየቱን፣ የተማሪዎች ቅበላ ስኬታማ እንዲሆን ኮሚቴ ተዋቅሮ እና ቀኑ ተወስኖ፣ የአዲስ ተማሪዎች መስከረም 28 እና 29/2012ዓ/ም የነባር ተማሪዎች ደግሞ መስከረም 22 እና 23/2012ዓ/ም ለመቀበል ዝግጅቱ መጠናቀቁን እንዲሁም በርካታ መሰል ስራዎች እንደተሰሩ አብራርተዋል፡፡
ከቅድመ ዝግጅት ስራዎች በተጨማሪ አዲስ ተማሪዎች ጎንደር ላይ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ቤተሰብ እንዲኖራቸው ለማድረግ የጎንደር ቤተሰብ የሚል ፕሮጀክት ተነድፏል፤ ይህ ፕሮጀክትም ተማሪዎች ጎንደር ላይ ከተፈጠሩላቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲገናኙ፣ባህሉን እንዲያውቁ እንዲሁም ቤተሰባዊ ቀረቤታ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ዶ/ር አስራት ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 86 ቅድመ መደበኛ ፣138 ድህረ ምረቃ፣ 23 የሶስተኛ ዲግሪ፣ 3 ሳብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች እየሰጠ እንደሚገኝ እና በ2012ዓም ደግሞ ከ20 በላይ በአዲስ የሚጀመሩ ፕሮግራሞች እንዳሉና ከእነዚህም መካከል የግዕዝ ቋንቋን ለመጀመር ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልፀዋል፡፡



