የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ሂሳብ ኦሎምፒያድ (UoG-MASO) ውድድር ፍጻሜውን አገኘ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የሳይንስና ሂሳብ ብቃት የሚያሳድግ የኦሎምፒያድ ውድድር ዛሬ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፤ የሁለተኛ ደረጃ ር/መምህራን እና ተማሪዎች በተገኙበት በፕሬዝዳንት አዳራሽ 6ኛ ፎቅ በይፋ ተጠናቀቀ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን አማካኝነት የተቀረጸው “University of Gondar Mathematics and Science Olympiad (UoG-MASO)” የተሰኘ አዲስ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት ከታህሳስ ወር ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ፕሮጀክቱ በጎንደር ከተማ በሚገኙ 18 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን የትምህርት አቀባበልና የፈተና ውጤት ለማሻሻል ያለመ ነው። ይህ የትምህርት ድጋፍ ለ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና በውድድር መንፈስ ተማሪዎች ውጤታቸውን ለማሻሻል ታስቦ የተቀረጸ ፕሮጀክት ሲሆን ማለትም ተማሪዎች በሂሳብ፣ በባዮሎጂ፣ በፊዚክስ እና በኬሚስትሪ ትምህርቶች ያላቸውን ክህሎት እንዲያሳድጉና ለብሔራዊ ፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ ታስቦ የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው።
የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አይንሸት አዳነ በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቶችና በተማሪዎች ላይ እንዲህ አይነት የማህበረሰብ አገልግሎቶች ተግባራዊ መደረጋቸው ለትምህርት ጥራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። “በትውልድ ላይ መሥራት” የሚል የኃላፊነት ስሜት በመኖሩ ፕሮጀክቱ ስኬታማ ሊሆን መቻሉን ጠቁመው፣ ለዛሬው በውድድር ለታጀበው ማጠቃለያ ፕሮግራም በመብቃቱ ለዩኒቨርሲቲውና ለፕሮጀክቱ አባላት በሙሉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ወደፊትም እንዲህ አይነቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽኖት ገልጸዋል።
የማህበረስብ አሳታፊነትና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም አድኖም በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተቀናጀ ሥራና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በከተማው የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማሳሳብ ለትምህርት ቤቶች ለጎንደር ከተማ ትምህርት መምርያ ለፕሮጀክቱ አባላትና በሥራው ላይ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋናና አድናቆታቸውን አቅርበዋል።
የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጂ ዲን ፕሮፌሰር ጌትነት ማስረሻ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ይህ አይነቱ ፕሮጀክት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው የማህበረሰብ አገልግሎቶች መካካል አንዱ መሆኑን ተናገረዋል፡፡ ፕ/ር ጌትነት አክለውም ይህ ፕሮጀክት ለሀገር የሚጠቅምና ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመግለጽ ለፕሮጀክቱን አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መምህር ሲሳይ አያናው እንደገለጹት፣ ውድድሩ በሶስት ዙር የተካሄደ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ፈተና 200 ምርጥ ተማሪዎች፣ በሁለተኛው ዙር 100 የሚሆኑ ምርጥ ተማሪዎች፣ በሶስተኛው ዙር ደግሞ ምርጥ 10 ተማሪዎችን በፈተና በመለየት በመጨረሻም ከ 1-3 የወጡ ተማሪዎች የተለዩበት ነው ብለዋል፡፡ መምህር ሲሳይ አክለውም፣ ይህ አይነት የውድድር መንፈስ ተማሪዎች በውጭ ሀገራት ለሚካሄዱ አለም አቀፍ የኦሎምፒያድ ውድድሮች እንዲሳተፉ የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል። በትምህርቱ ሂደት በከተማው ከሚገኙ 18 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 15ቱ በንቃት የተሳተፉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ወንድ 570፣ ሴት 498 በድምሩ 1,068 ተማሪዎችን ማሳተፍ ተችሏል።

በመጨረሻም በዶ/ር አይንሸት አዳነ እና በዶ/ር ክብሮም አድኖ ከ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ትምህርት ቤት የወርቅ እና የብርና ሜዳሊያ እንዲሁም የ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቀው የአዘዞ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የነሀስ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት በተጨማሪም የጽህፈት መሳሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ከ 4-10 ለወጡ ተማሪዎች ደግሞ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን በፕሮፌሰር ጌትነት ማስረሻ እና የማህበረሰብ አሳታፊነት አስተባባሪ በሆኑት በመ/ር ተመስገን አያልነህ አማካንነት የሰርተፊኬትና የጽህፈት መሳሪያ ተበርክቶላቸዋል፡፡
*************
ለልህቀት እንተጋለን!
የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ
ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
See less



